ስለምን እንሰቃያለን?
ስለምን ስቃያችን በዛ?
✍★✍
ሁላችንም እንደምናውቀው ከጊዜ ወደ ጊዜ ከዘመን ዘመን የሰው ልጅ ህይዎት እጅግ እየተሻሻለ ነው። ይሁን እንጅ ይህ የኑሮ ወይም የህይዎት መሻሻል ለሁሉም ሰዎች እኩል ሊሆን አልቻለም። በእርግጥ እኩል እንዲሆን አይጠበቅም። ነገር ግን ተመጣጣኝ ይሆን ዘንድ አስፈላጊ ነው። በአንድም በሌላም ምክንያት ግን ሰዎች የመረረ የስቃይ ሕይዎትን እያሳልፉ ነው። ለምን?ስለምን እንሰቃያለን?
እንደኔ ዕይታ ለዚህ ጥያቄ መልሱ “ከተፈጠርንበት ዓላማ ስላፈነገጥን” ይመስለኛል። ነውም። የተፈጠርነውስ ለምንድን ነው?እንግዲህ በሁለቱ ታላላቅ ሀይማኖቶች ማለትም እንደ እስልምና እና ክርስትና አስተምህሮ የሰው ልጅ የተፈተረው ፈጣሪውን በምስጋና ሊያገለግል ነው። በተለይም እንደ ክርስትናው አስተሳሰብ ሰው በፈጣሪው አርአያ ከአራት ባህርያተ ሥጋና ከሦስቱ ባህርያተ ነፍስ ተፈጥሮ አምላኩን እያመሰገነ በኤደን ገነት ይኖር ዘንድ ተፈጠረ። ነገር ግን በመጀመሪያው ሰው አዳም በተለይም ከጎኑ በተገኘችው ሄዋን አዕምሮ ውስጥ ከንቱ መሻት ሰረጸባቸው። አምላክ መሆንን የሁሉ ገዥ መሆንን ተመኙ። ያን ጊዜም ጥፋትን አጠፉ። ለቅጣትም ከገነት ወጥተው ወደ ምድር ተጣሉ።
ይህ ታሪክ ምናልባትም ያለፈ የተረሳና ርባና ቢስ የሆነ አፈታሪክ ሊመስለን ይችላል። በእውነት ቆም ብለን ብናስተውል ግን ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ላይ እየተካሄደ ያለ ክስተት ነው። የሰው ልጅ በምድር ላይም እየኖረ የቀድሞው ከንቱ ምኞቱ ያ ገዥ የመሆን የበላይ የመሆን ምኞቱ ዛሬም ከልቦናው ውስጥ አልታጣም። ይህ ምኞት ደግሞ ሰውን ለአውሬው ተገዥ ባሪያ ለማድረግ የተጠመደ ወጥመድ ወይም አሽክላ ነው። ዛሬም ህልማችን የበላይ መሆን ነው። ዛሬም ምኞታችን አለቃ መሆን ነው። ተገቢው እውቀት፣ ብቃትና ልምድ ይኑረንም አይኑረንም የምንፈልገው አንድና አንድ የበላይ መሆንን ነው። በምጣኔ ሀብትም፣ በፖለቲካውም፣ በማህበራዊ ሕይዎታችንም እኛን የሚበልጠን እንዲኖር አንፈልግም።በእድሜያችን፣ በአቅማችን ወይም በብቃታችን ልክ ለመኖር ቅንጣት ታክል መሻት የለንም። ይሄንንም ከንቱ ምኞታችንን ለማሳካት የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። በአቅማችን ውስንነት ወይም በሌላ ተገቢ ምክንያት ሀሳባችን ሳይሳካ ሲቀር ከትክክለኛው አካሄድ እንወጣለን። ያን ጊዜም በሌሎች ሕይዎት ውስጥ ጣልቃ እንገባለን። ኅልውናቸውንም አደጋ ላይ እንጥለዋለን። የእኛን ዳቦ ለማብሰል ብለን የሌሎችን ቆሎ እንደፋለን። እኛ እንድንስቅ የሌሎችን ደስታ ወደ ሀዘን እንለውጣለን። የእነርሱንም ሳቅ በመስዋዕትነት እናቀርባለን።
የኛ ቤት ብርሀን እንዲሆን የሌሎችን ቤት እናጨልማለን። ያን ጊዜም ስቃይ በሰዎች ዘንድ ይበረታል። ፍቅርም ከሰዎች መካከል ትጠፋለች። ሁከት ለቅሶና ወይወይታ ይበዛል።
ልናስተውል ይገባናል። አንድ ቀን ራሳችን የገረፍነው ጅራፍ ጩኸቱ የጆሯችንን ታምቡር ሊበሳው ይደርሳል። ራሳችን የገነባነው ጡብ ይናድና በላያችን ላይ ይወድቃል። ራሳችን ያሰመርነው ክልል ራሳችን የከለልነው ድንበር ራሳችን የሰራነው አጥር እኛኑ መንቀሳቀሻ ያሳጣንና እኛኑ መውጫ ያሳጣንና በሆነ አጋጣሚ በሚነሳ እሳት ዐይናችን እያየ እንቃጠላለን። ለሌሎች በገነባነው ማጎሪያ እኛው እንገባበታለን። የሌሎችን አፍ እንዳፈንን እኛም የምንታፈንበት ቀን ይመጣል። እንጀራቸውን ያሳረርንባቸው፣ ቤታቸውን ያጨለምንባቸው፣ ደስታቸውንና ነጻነታቸውን የቀማናቸው ሰዎች ሁሉ ከጊዜ ጋር ተባብረው የሥራችንን ዋጋ ይከፍሉናል። ሁሉም የእጃችንን ይሰጡን ዘንድ ወደ እኛ ይመጣሉ። የዘራነውን እናጭዳለንና። ያን ጊዜም እነርሱን ቀና ብለን የምናይበት ዐይን፣ እነርሱን ደፍረን የምናናግርበት አንደበት፣ ድምፃቸውን የምንሰማበት ጆሮም አይኖረንም።
እውነት እውነት እላችኋለሁ! እኛ በትንሣኤ ሙታን የምናምን ሰዎች ከዚህ ሁሉ ልንጠነቀቅ ይገባናል። ለተፈጠርንበት ዓላማ ልንኖር ግድ ይለናል። ፈጣሪን ካስደሰትነው ሰውን ልናስከፋ አንችልም። ሥለዚህ ሁልጊዜም ቢሆን በሚመች አካሄድ እንራመድ። እርስ በርሳችን በፍጹም ፍቅር እንዋደድ። ማንንም አናስቀይም። ይቅር እንባባል። ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን በተግባር እንስበክ። በተለይ እኛ ኢትዮጵያዊያን የሚያምርብን ፍቅርና አንድነት ነው። ከታሪካችን የምንማረው አንድ ስንሆን እንደምናሸንፍ ነው። ስለዚህ ዘር ሐይማኖት ቋንቋ ሳይገድበን ሁሌም በፍቅር አንድ እንሁን። መንግስትን ከመታገላችን አስቀድመን በመካከላችን ያለውን ጥላቻና ቅራኔ እንታገል። ያኔ አንድ ስንሆን እንኳን ለውስጥ ጠላት ቀርቶ ለውጪ ኃይል እንኳን የማንበገር እንሆናለን። ፈጣሪን ሳንረሳ ለተፈጠርንበት ዓላማ በፍቅርና በአንድነት ብንቆም ኖሮ ስቃይና ችግር ከእኛ ጋር ባልሆኑ ነበር።
(በፍጥነት ስለፃፍኩት ማለት የፈለግሁትን እያረማችሁ እንዳነበባችሁት ተስፋ አለኝ!)
መጪው ጊዜ እስር ቤቶችና ሆስፒታሎች ሁሉ ሰው አልባ የሚሆኑበት እና በአንድነታችን ጠላቶቻችንን ሁሉ የምናንበረክክበት ይሁንልን፥ አሜን።
ዘጸአት ለኢትዮጵያ!
ሀሳባችሁን ጻፉልኝ እንማማር።
www.facebook.com/danethiop
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ