ለባርነት የተዘጋጀ ትውልድ
>>>>=========<<<<
ዓለማችን ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ አዕላፍት ትውልዶች አልፈዋል። ትውልድ ማለት በአንድ ወቅት ወይም በተመሳሳይ ጊዜ የተወለደና በተመሳሳይ ወቅት
የሚኖር የማህበረሰብ ስብስብ ማለት ነው። አባታችን አዳም የመጀመሪያው ሰው እንደሆነ የተለያዩ የሀይማኖት መዛግብት ይናገራሉ። ይሄን ስል ግን አንድ ጥያቄ
በአዕምሮዬ መጣ። እውነት ግን ዛሬ በዓለማችን ውስጥ የሚኖሩት ህዝቦች ሁሉ የዘር ግንዳቸው አንድ ነውን? ታዲያ ምን ለያያቸው? በጣም ነው የሚያሳዝነው።
ትናንት ከአንድ ዘር ከአንድ አባት ተፈጥረን ዛሬ በየራሳችን ዓለም ውስጥ እየኖርን እኛው ራሳችን ድንበርና ክልል አበጅተን አንዳችን የበላይ ሆነን የራሳችንን ጥቅም
ለማስቀደም ስንል ሌላኛውን የበታች አድርገን ለመጨቆን በምናደርገው ትግልና ጥረት ምክንያት እርስበርሳችን አቤልና ቃዬልን ሆነናል። ለዚህም ነው በቋንቋ፣ በቀለም፣ በቦታ፣ በሀይማኖት ተከፋፍለን አጥፊና ጠፊ የሆንነው። ምን ይሆን
የሚሻለን? ምን ይሆን ከዚህ ካለንበት የቆሸሸ አካባቢ የሚያወጣን?
በዚህ ጽሁፌ እኔ ስላለሁበት ትውልድ (እኔንም ጨምሮ) የታዘብኩትን አንዳንድ ትዝብቴን ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ። ስለዚህ ትዝብቴን ብጥሞና ትታዘቡልኝ ዘንድ
እጋብዛለሁ። እኔ በእድሜ የ20ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ እገኛለሁ። ይህ ማለት ደግሞ ሁለት አስርት አመታትን አስተናግጃለሁ ማለት ነው። አቤት እድሜ ግን
እንዴት ነው የሚሮጠው? እንደዋዛ እኮ ሃያ አመታትን አሳልፌያለሁ። ወይ ግሩም። የሚገርመው ግን ይሄ አይደለም እነዚህን አመታት ያለምንም ፍሬ ማሳለፌ ነው እንጅ። እናም ወደ ዋናው ጉዳዬ ስመለስ በእነዚህ ባሳላፍኳቸው
ሁለት አስርት አመታት ግን እንደአቅሜ ብዙ ነገሮችን ተመልክቻለሁ። ያው መመልከት ብቻ። ታዲያ ማስተዋልንማ ማን ያስተውላል። ማስተዋል ድሮ ቀረ። የዛሬ ትውልድ ማስተዋልን የሚያውቀው ምናልባት የሰው ስም ሆኖ ብቻ እንጅ በተግባር ግን አያውቀውም። ይሄን ስል ግን ካየሁት አንጻር ብዙኃኑን ለማለት ነው እንጅ ሙሉ በሙሉ የትውልዱን አባላት ሁሉም አያስተውሉም ማለቴ አይደለም። ምክንያቱም ጥቂት የማይባሉ ማስተዋልን የታደሉ የትውልዱ አካላት
አሉ። አሁን የአንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በእንግሊዝኛ አጠራሩ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነኝ። በዚህ ባለሁበት ተቋም ውስጥ ከመደበኛው ትምህርት ውጪ ብዙ ሊባል የሚችል የህይዎት ትምህርትን ተምሬያለሁ። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትንሿ ኢትዮጵያ እንደመሆናቸው መጠን ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍላት ከመጡ ተማሪዎች የተለያዬ ባህል፣ ባሕሪይ፣ ቋንቋ ሀሳብና ማንነት ለመማር ችያለሁ። የሰው ልጅ ልክ መልኩ እንደሚለያየው ሁሉ አስተሳሰቡም ሆነ አተያዩ እጅግ በጣም ይለያያል። አንዳንዱ የዋህ ሌላው ክፉ፣ አንዳንዱ አስተዋይ ሌላው ችኩል፣ አንዳንዱ በአዕምሮው የሚያስብ ሌላው ደግሞ በጉልበቱ፣ አንዳንዱ ነገን የሚያስብ ሌላው ደግሞ ዛሬን ብቻ፣ አንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሌላው (ብዙኃኑ) ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ግን በደም እንጅ በስራውና በአስተሳሰቡ ኢትዮ ጵያዊ
ያልሆነ ኧረ ስንት አይነት ሰው አለ። በተለይ ይሄን ትውልድ ላስተዋለው እያለ የሌለ በቁሙ የሞተ ትውልድ መሆኑን ሲረዳ ምን ያክል ልቡ እንደሚያዝን አስቡት።

ይህ ትውልድ ካለፉት አዕላፍት ትውልዶች የሚለይበት እጅግ በጣም ብዙ መጥፎም ጥሩም ባህሪይ አለው። ከመጥፎው ስጀምር ትውልዱ ማንነቱን ያጣ፣ ከሰውነት የወጣ፣ ህሊና ቢስ፣ ጨካኝና አረመኔ፣ ከምንም ነገር በላይ ለገንዘብ የሚሞት፣ ከእግዚአብሔር አምልኮ የወጣ፣ አዕምሮውን ዘርና ጎሳ በሚባሉ ትቢያዎች የሞላ፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩ ነትን የሚናፍቅ ወዘተረፈ የትውልዱ ጉድ በእኔ አቅም ተዘርዝሮ አያልቅምና እዚህ ጋ ላብቃ። ወደ ጥሩ ባህሪዎቹ ስቀጥል ደግሞ አዲስ ነገርን ለማወቅ ፅኑ ፍላጎት አለው። አንድም ቀን ግን ቆም ብሎ መጥፎም ይሁን መልካም ባህሪዎቹን አስተውሎ አያውቅም። ማስተዋል የለማ። ከየት ይመጣል? ንገሩኝ እስኪ ማስተዋል ከየት ይመጣል? ለመሆኑ ለዚህ ትውልድ መጥፋት ተጠያቂው ማን ነው? አንድ አትክልተኛ አንዲትን ተክል ሲያሳድጋት ከጅምሩ ካጣመማት መጨረሻ ካደገች በኋላም ጠማማ ነው የምትሆነው። መጀመሪያ ግን እንዳትጣመም ተንከባክቦ ካሳደጋት ያች ተክል ካደገች በኋላም ያው ቀጥ እንዳለች ነው የምትኖር። ልክ እነደ አትክልተኛው ወላጅ ልጁን ሲያሳድግ ከፍተኛ ሀላፊነት አለበት። አንድ ወላጅ ልጁን ሲያሳድግ ስለመጥፎ ነገር እያስተማረና መጥፎ ነገርን እንዲያደርግ
እየመከረ ካሳደገው ያ ልጅ ካደገ በኋላ መልካምነትን ከየት ያመጣዋል? እርሱ የሚያውቀው እኮ ክፉ መሆንን ብቻ ነው። ምክንያቱም ወላጁ ሲያሳድገው በአዕምሮው እንዲቀረፅበት ያደረገው መልካምነትን ሳይሆን ክፉነትን ነው። ታዲያ
ለዚህ ተጠያቂው ማን ነው? ወላጁ ነው ወይስ ልጁ? ታዲያ ይህ እኔ ያለሁበት ትውልድም እኮ ከዚህ የተለየ ማንነት የለውም። እኔ ብዙ ጊዜ ግራ የሚያጋባኝ ነገር ይህ ነው። ትውልዱ በቁሙ እንዲሞት ያደረገው ማን ነው? ራሱ ትውልዱ ነው ወይስ የትውልዱ ወላጅ? ህፃናት ማለት ነጭ ወረቀቶች ናቸው። የጻፉባቸውን ነገር ወዲያውኑ ይቀበላሉ። “ሞኝና ወረቀት የያዘውን አይለቅም” እንደሚባለው እነርሱም መጀመሪያ የተፃፈባቸውን ይዘው ያድጋሉ። ሲያድጉም
የራሳቸውን የተሳሳተ መሻት ይጨምሩበትና የተበላሸ ማንነትን ይይዛሉ። እነዚህ ናቸው እንግዲህ ትውልድ የሚባሉት። ተጣምሞ ያደገ ያው ጠማማ ይሆናል። ተስተካክሎ ያደገ ደግሞ መልካም ይሆናል።

አንድ እውነተኛ ታሪክ ልንገራችሁ። በመዲናችን አዲስ አበባ የተለያዩ ጭፈራ/ ዳንኪራ ቤቶች አሉ። እናም ከእነዚህ ቤቶች በአንደኛው ምን ተፈጠረ መሰላችሁ ቤቱ ውስጥ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች መግባት አይችሉም። ታዲያ አንድ
ቀን አንዲት ቀበጥ ህጻን ልትገባ እያለ ዘበኛው መግባት አትችይም ይላታል። ለምን? ስትለው አይ እዚህ ቤት ውስጥ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ መግባት ስለማይችሉ ነው ብሎ መለሰላት። በዚህ ጊዜም ህጻኗ አባቷ ጋ ትደውልና “ሄይ
ዳድ መግባት አልቻልኩም እኮ። በሩ ጋ ያለው ጋርድ አላስገባሽም አለኝ” አለችው። አባትዬውም “ኋት? ለምን? በቃ ጠብቂኝ እዚያው እመጣለሁ” አላትና ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መጣ። ከዚያም ማን ነው እንዳትገቢ የከለከለሽ?
ያ ሰውዬ ነዋ ዳድ(በጣቷ ዘበኛውን እየጠቆመች)
ለምን?
እኔ እንጃ። ከ18 አመት በታች ያሉ ህጻናት መግባት አይችሉም ምናምን አለኝ።
ለምን? ምንስ አገባው? እያለ ወደ ዘበኛው ሄደና “ለምንድን ነው ልጄን እንዳትገባ የከለከልካት?” አለው ዘበኛውን
ዘበኛውም “ይቅርታ ጌታዬ ህጻናት እንዳይገቡ ስለተባልኩ ነው። ደግሞ እስከዛሬም ቢሆን ከ18 ዓመት በታች ያሉ ሰዎች ገብተው አያውቁም። እኔ ታዛዥ ነኝ ጌታዬ። ደግሞም በእውነቱ ከሆነ ለዚህች አንድ ፍሬ ህጻን ዳንኪራ ቤት ምን
ይጠቅማታል?”
“አንተ ስለሱ ምን አገባህ? በል አሁን ዞርበል ልጄ ትግባበት” ብሎ አባት ልጁን ጭፈራ ቤት አስገባት። ታዲያ ማን ነው ተጠያቂው?

አቤት ይህ ያለሁበት የትምህርት ተቋምማ ስንቱን ጉድ ነው የሚያሳየኝ። በእውነት አንዳንዴ ሳስበው የዚህ ትውልድ አካል በመሆኔ ብቻ ራሴን እረግማለሁ። ባልተፈጠርኩ ብዬም ወደ ፈጣሪ እሄዳለሁ። ተመልክታችሁታል ግን? ትውልዱ እኮ ትህትና፣ ሰብዓዊነት፣ ጽኑ እምነት (በተግባርና በስራ የተደገፈ)፣ ንፁህ ፍቅር (ከወረት የጸዳ)፣ መልካምነት፣ ሀቀኛነት፣ ሰው አክባሪነት፣ አስተዋይነት፣ ንጹህ ማንነት (ከምዕራባውያን ጫና የጸዳ ሀበሻዊ ማንነት)፣ ችግር ፈችነት፣ ታጋሽነት፣ ጥበብ እና የመሳሰሉት እሴቶችን ፈፅሞ
አያውቅም። አቤት የፈጣሪ ያለህ። ታዲያ ይሄ ትውልድ አለ ነው እንዴ የሚባለው? የለም እኮ ሞቷል።
ይህ ትውልድ እያለ በቁሙ የሞተ ትውልድ ነው። የተፈጠረውም ለባርነት ነው። ምክንያቱም ላስተዋለው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው የሚያሳየው ትውልዱ
ምን ያክል በምዕራቡ ባህል እንደተወሰደ ነው። ምንም የማይጠቅም ትውልድ ቢኖር ይህ ትውልድ ነው። ለዚህ ደግሞ ከፍተኛውን ሚና የተጫዎተው (ምሁራን ነን ባዮች እንዳሉት) ሉላዊነት ነው። ሉላዊነት ከወቅቱ የቴክኖሎጂ እድገት ጋር ተባብሮ የሀገራችንን ትውልድ እያጠፋ ነው። ማህበራዊ መገናኛዎችም የዚህ ጥፋት አንቀሳቃሽ ሞተሮች ናቸው። ግን ሉላዊነቱን አሜን ብሎ የተቀበለው ማን ነው? እኛው አይደለን? ማን አስገደደን? ታዲያ ይበለና። የስራችንን ነው እያገኘን ያለነው። አንድን ትውልድ መቅረጽ ከሚችሉ አካላት አንዱና ዋነኛው መንግስት ነኝ የሚለው አካል ነው። መንግስትን ደግሞ መምራት ያለባቸው ከህዝቡ የወጡ ለህዝቡ የሚያገለግሉ ሰዎች መሆን አለባቸው። ይህ ካልሆነ ግን ያው አሁን እንደምናየው እያለ የሌለ ትውልድ ይፈጠራል ማለት ነው። አንድ መንግስት ማድረግ ከሚገባው ኃላፊነቶች አንዱ የህዝቡን ባህል፣ ቋንቋ፣ ቅርስ፣ ማንነት፣ ታሪክና የመሳሰሉትን እሴቶች መጠበቅ ነው። ይሄን ካላደረገ ግን መንግስት ሳይሆን ወራሪ ነው። እኛ ሀገር ውስጥም እያየን ያለነው ይህን ነው።
ለምሳሌ
ከእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ወይም በአቅራቢው መጠጥ ቤቶች፣ ጫትና ሲጋራ ቤቶች፣ ሺሻ ጋንጃና ጭፈራ ቤቶች ይከፈታሉ። ይህ ደግሞ ትውልዱን ለመበከል ከፍተኛውን ሚና እየተጫወተ ነው። በአንድም በሌላም
መንገድ ወጣቶችና ህፃናት ወደሱስ ውስጥ ይገባሉ። ታዲያ እነዚህን የሱስ ቦታዎች አጥንቶና መርምሮ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ያለበት ከመንግስት ውጭ ማን ነው? ለነገሩ ከጎጂ እፆች አንዱ የሆነውን ጫትን ህጋዊ አድርጎ
ከፈቀደ መንግስት ይሄን መጠበቅ ሞኝነት ነው። ይህ ስራው እኮ መንግስታችንን በአለም ላይ ካሉት መንግስታት መካከል የመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ውስጥ ያስገባዋል። ወይ ኢትዮጵያ!!!
በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ከምንም በላይ እየተስፋፋና እየጨመረ የመጣ ነገር ቢኖር የሱስ ቦታዎችና የሱሰኞች ቁጥር ነው። ሰሞኑን የሰማሁት አንድ መረጃ የኢትዮጵያ ሃያ በመቶ (20%) ሕዝቧ በአጉል ሱሶች የተጠመደ ነው ይላል። ምክንያቱም በእነዚህ ቦታዎች ላይ ምንም አይነት እርምጃ እየተወሰደባቸው አይደለም። ይሄ ደግሞ ትክክለኛውን የመንግስትን ዓላማ ያስረዳል። ማለትም መንግስት ትውልዱን በሡስ በማደንዘዝና በማጀዘብ ለስልጣኑ ተቀናቃኝ የሚሆን ትውልድ እንዳይፈጠር በማድረግ የስልጣን ጊዜውን ማስረዘም ነው ዓላማው። ለዚህም ያግዘው ዘንድ በተለያዩ የትምህርት ተቋማት አቅራቢያ የሱስ ቤቶች እንዲከፈቱ ፈቃድ በመስጠት የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ህፃናትንና ወጣቶችን ያጠምዳል። እስኪ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው (ተመርቀው ለማለት እንኳን ይከብዳል። ምክንያቱም ከወጡ በኋላ ስራ የለም) የሚወጡ ሰዎችን ተመልከቱ። ሃምሳ ከመቶ በላይ የሚሆኑት ሱሰኞች ናቸው። ለምሳሌ እኔ በምማርበት ትምህርት ክፍል አጠቃላይ አንድ መቶ ሃያ ተማሪዎች ነበርን። ዛሬ (ከ4 ዓመታት በኋላ) ግን
ዘጠና ደርሰናል። ከዘጠናዎቹ መካከልም ከሃምሳ በላይ የሚሆኑት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሱሰኞች ናቸው። እንግዲህ ይህን ያክል ነው ትውልዳችን እየጠፋ ያለው። ኢትዮጵያዊነት የሚባል ስሜትና ወኔ ከትውልዱ ህሊና የለም። ሁሉም ኬሬዳሽ ነው። ታዲያ ነገ ይህችን ሀገር የሚታደጋት ማን ነው? ትውልዱ ለባርነትና ለሸክም የተፈጠረ ትውልድ ሆኗል። በአንድም በሌላም መንገድ ራሱን በምዕራባዊያን ባህል እየተበተበ የራሱን ማንነት እየገደለ ነው ያለው። ዛሬ ስለ አድዋ የምኒሊክ ድል ከምታወራው ሞቱን ይመርጣል። ስለ የካቲት 12 ከምትጠይቀው ይልቅ ስለ ቢዮንሴ፣ ክሪስ ብራውንና ሌሎች የሰይጣን አምላኪዎች ብትተርክለት ይደሰታል። ከአረንጓዴ ቢጫ ቀይ አርማችን ይልቅ የአሜሪካ ባንዲራ ነው ልቡ ውስጥ የሚገኝ። ስለ በላይ ዘለቀ፣ አብዲሳ አጋና ሌሎች የሀበሻ የቁርጥ ቀን ልጆች ከምታወራለት ይልቅ የቦብ ማርሌይን የክርስትያኖ ሮናልዶን ታሪክ ብትዘረዝርለት ይመቸዋል። አባቶቻችን ዋጋ ከፍለው ያቆዩትን ማንነቱንና ነጻነቱን በራሱ ፈቃድ እያጣና በባርነት ስር እየወደቀ ነው። የተፈጠረበትን ዓላማ ረስቷል።

እስኪ በየአካባቢያችሁ ያሉትን ሆቴሎች፣ መጠጥ ቤቶች፣ እንግዳ ማረፊያዎች፣ መዝናኛዎች፣ ዳቦ ቤቶች ወዘተ ጠጅ ቤቶችን ሳይቀሩ ተመልከቱ። የሚጠሩበት ስም ከየት የመጣ ነው? ኢትዮጵያዊ ነውን? በፍጹም አይደለም። ኒው ዮርክ፣ ዳላስ፣ ቴክሳስ፣ ስቶኮልም፣ ዋሽንግቶን የመሳሰሉ ስሞችን ነው የምታገኙት። ይህ ደግሞ ህዝባችን ምን ያክል በባርነት ውስጥ እንዳለ ነው የሚያሳየው። እጅግ በጣም ያሳዝናል። አባቶች ደማቸውን አፍስሰው፣ ስጋቸውን ቆርሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰውና የህይዎት መስዋዕት ከፍለው ከምዕራባዊያን ቅኝ ግዛት ነፃ አውጥተው ከነባህሏና ማንነቷ ካስረከቡን ሀገር ውስጥ ይሄን መሳይ ትውልድና ህዝብ ማዬት በጣም ያሳዝናል ያሸማቅቃልም። እንመለስ። ዛሬ ላይም አልረፈደብንም። ወደ ራሳችን እንመለስ። ካለንበት ባርነት ነፃ እንውጣ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ዘጸአት ለኢትዮጵያ!
አሜን።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች