ይድረስ ለአርቲስቶቻችን
የትኛው ይቀድማል?
እኔ ሁሌም በጣም የሚገርመኝ አንድ ነገር አለ። እነዚህ አርቲስቶቻችን በየሚዲያው ሲቀርቡ አንድ ደጋግመው የሚናገሩት ነገር አለ። ሁሉም ስለቅጂ መብት ያወራሉ። ህዝቡንም ዋናውን ቅጂ [ኦሪጅናሉን] እንዲገዛ ያሳስባሉ። በዚህም ብቻ አይመለሱም። ማኅበረሰቡ ስለቅጂ መብት ምንም አይነት እውቀት እንደሌለው ደጋግመው ይገልጻሉ።
ለመሆኑ ስለየትኛው ሥራቸው ነው የሚያወሩት? ደግሞስ ስለቅጅ መብት መለፍለፍ ነው ወይስ ጥሩ ሥራ ሰርቶ  ማቅረብ ነው የሚቀድመው? የትኛው ይቀድማል? እንኳን ኮፒ ተደርጎ  በነጻ እንኳን ሊታይ ወይም ሊደመጥ የማይችል ተራ ሥራ እያቀረቡ ስለቅጅ መብት መለፍለፍን ምን ይሉታል? እስኪ የዘመኑን ሙዚቃ እንመልከት። ወይ ግጥሙ አይጣፍጥ፣ ወይ ዜማው አይማርክ ወይ ደግሞ ቪዲዮ ክሊፑ ኢትዮጵያዊ ቃና የለው። ምኑም የማይጣፍጥ ሥራ እያቀረቡ አርቲስት ተብለው ሲጠሩ አለማፈራቸው በጣም ይገርመኛል። ሙሉ በሙሉ ከውጭ ኮርጀው ያመጡና በራሳቸው ፈጥረው እንደሰሩት ሕዝቡን ዋናውን ቅጅ ግዛ እያሉ ሲናገሩ ስሰማ ያናድዱኛል። እነርሱ እየኮረጁ የተኮረጀ አትግዙ ማለት ምን ማለት ይሆን? ማንም እየተነሳ ይጮህና አርቲስት ይባላል። በውኑ የጮኸ ሁሉ አርቲስት ነውን? ምናለ የከበረውን ሙያ ባታረክሱት? ሌላ ስራም እኮ ሞልቷል ሥራ መቀየር ካስፈለጋችሁ። የህዝብን ስሜት መግለጽ ሳይችሉ፣ እንዲሁም ከህዝብ ጎን መቆም ሳይችሉ የህዝብ ልጅ ነኝ፣ ሀብቴም ንብረቴም ሕዝቡ ነው እያሉ ማላዘን ተገቢ አይደለም።
ተዋንያንያንን እንመልከት። ገንዘብ ከተከፈላቸው ምንም አይነት ፊልም ከመስራት ወደኋላ አይሉም። ተዋንያኖች ሆይ እስኪ ከመተወናችሁ በፊት የፊልሙን ጭብጥ መርምሩት። ለማህበረሰቡ ያለውን አወንታዊና አሉታዊ ፋይዳ አጥኑት። ተዋናይ ነኝ ብላችሁ ስላሰባችሁ ብቻ የወረደ ስራ ሰርታችሁ ፊልም ብላችሁ አትስጡን። በተለይ ደራሲዎች ራሳችሁን መርምሩ። የምትደርሱት የፊልም ጽሁፍ የገሃዱ ዓለም ነጸብራቅ መሆን መቻል አለበት። ይሄ ሲባልም የማሕበረሰባችንን አመለካከት በበጎ መቀየር የሚችል፣ የሕዝባችንን ባህልና ማንነት የሚያዳብር፣ በሰዎች መካከል ጤናማ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲኖር የሚያስተምር፣ ፍቅርን እውነትንና መልካምነትን የሚሰብክ፣ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ስለእናት ሀገሩ ያለውን ስሜትና ፍቅር የሚያጎለብት፣ የህዝብን ብሶት የሚገልጽ ወዘተ አይነት የፊልም ጽሁፍ ነው መጻፍ የሚገባችሁ። ከዚህ ውጪ ግን እስካሁን እንዳሳያችሁን ተራና እርባና ቢስ የሆነ  ሥራ ከምታቀርቡልንና ጊዜአችንን እንዲሁም ገንዘባችንን በከንቱ ከምታጠፉ የሀገሪቱን የፊልም ኢንደስትሪ እያቀጨጫችሁት ነውና ዛሬውኑ ሥራ ቀይሩ። ራሳችሁን ከዚህ ታላቅ ሙያ አግልሉ።
ደግሞ ከማንም አትኮርጁ። የራሳችሁን የፈጠራ ውጤት ለማቅረብ ሞክሩ። ከዚህ ውጪ ግን እባካችሁ አርፋችሁ ተቀመጡ። አታሳፍሩን።
በአንድ ወቅት የተለያዩ ተዋንያን ስለቅጂ መብት [ኮፒ ራይት] የሰጡትን አስተያየት እየተመለከትሁ ነበር። እናም ከአርቲስቶች መካከል አንዱ ሲናገር የሀገራችን የፊልም ኢንደስትሪ አድጎ ኢትዮጵያም የራሷ የሆነ ኢትዮሊውድ የተባለ [የሚባል] የመዝናኛ ኢንደስትሪ እንዲኖራት እፈልጋለሁ ነበር ያለው። እርሱ እንደዚህ ለተናገረ እኔ በጣም ነበር የተሸማቀቅሁት። ሁላችሁም እንደምታውቁት ከአሜሪካው ሆሊውድ፣ ከሕንዱ ቦሊውድና ከናይጄሪያው ኖሊውድ የተኮረጀ [የኮረጀው] ስም ነው ኢትዮሊውድ። ትርጉም የሌለው ስያሜ። አሁን ይሄ በውኑ የጥበብ ሰው ነውን? አይመስለኝም። ምናለበት ኢትዮጵያዊ ቃል ቢጠቀም?ቋንቋ አልቸገረን፣ ቃላት አልቸገሩን። የሌሎችን ስያሜ መኮረጁ ለምን አስፈለገ? አሁን ይሄ የሕዝብ ልጅ ነኝ ከሚልና የብዙ ዓመት የሥራ ልምድ ካለው ዝነኛና ኢትዮጵያዊ ከሆነ አርቲስት የሚጠበቅ ነው?ከዚህስ በላይ የሚያሳፍር ንግግር ይኖር ይሆን? በእውነቱ በጣም አፈርኩበት።
ሌላው ነጥቤደግሞ ሁሉም አርቲስቶች ለምን ጥሩ ስራ ማቅረብ እንዳልቻሉ ሢጠየቁ የሚሰጡት ምላሽ ነው። ሁሉም የምጣኔ ሀብት አቅም ማነስ ወይም የገንዘብ እጥረት ወዘተና ሌላ ተልካሻ ምክንያት ነው የሚሰጡት። አንዳቸውም የብቃት ማነስ ሲሉ አልሰማኋቸውም። በዚህ ዘመን አንድ ሥራ ለመስራት በእርግጥ ገንዘብ ትልቅ ሚና አለው። ነገር ግን የኛዎቹ አርቲስቶች ባላቸው ገንዘብ እንኳን ጥሩ ሥራ ሰርተው ማቅረብ አልቻሉም። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ገንዘብ ቢያገኙም አሪፍ ስራ መስራት አይችሉም ማለት ነው። የገንዘብ እጥረት ወይም የምጣኔ ሀብት አቅም አለመኖር የወረደ የፊልም ጽሁፍ ለመጻፍ፣ ምኑም የማይጣፍጥ ዘፈን ለመዝፈን፣ እርባና ቢስ የሆነ ፊልም ለመሥራት ወዘተ በፍጹም ምክንያት አይሆንም። ይሄ በተዓምር ምክንያት ሊሆን አይችልም። የአዕምሮና የብቃት እጥረትን በገንዘብ እጥረት መሸፈን እጅግ በጣም አሳፋሪና ነውር ነው።
እስኪ ወደኋላ እንሂድና እንመልከት። የድሮ ዘፋኞች እኮ ዘመን ተሻጋሪ ዘፈን የዘፈኑት ገንዘብ ስላላቸው አይደለም። እንደውም ከእነርሱ ይልቅ የዛሬ ዘፋኞች የተሻለ የገንዘብ አቅም አላቸው። ነገር ግን ከአንድ ቀን በላይ ሊደመጥ የሚችል አንድም ዘፈን አውጥተው አያውቁም። እንኳን ዘመናትን የሚሻገር ዘፈን ይቅርና ወራትን የሚሻገር ዘፈን መሥራት አይችሉም። ለምን ይሆን?ምንም አቅም ስለሌላቸው ነዋ። ታዲያ ለምን ዘፋኝ ሆኑ? እውቀት ስለማይጠይቅና በቀላሉ ዝነኛ መሆን ስለሚያስችል ብቻ። ዛሬ እኮ የዘፋኙ ብዛት ቢቆጠር የሀገሪቱን አንድ ሁለተኛ [ግማሽ] ሕዝብ ሊሆን ምንም አልቀረውም። ተጋነነ? ምን ላድርግ ዘፋኞች እጅግ በጣም መብዛታቸውን አስረግጬ ለመናገር ፈልጌ እኮ ነው። ያም ሆነ ይህ የዘፋኝ መብዛት የዘፈን ጥራታን አያመጣም ለማለት እፈልጋለሁ። ለማንኛውም አርቲስቶች ሆይ! የተዋጣለት ስራ ለመስራት ሞክሩ። ያኔ ሕዝቡን ኮፒውን ግዛ ብትሉት እንኳን ራሱ ኦሪጂናሉን የትም ፈልጎ ይገዛል እንጅ በጭራሽ ኮፒውን አይገዛም። የኢትዮጵያን ሕዝብ አታውቁትም እንጅ እናንተ የሚጠበቅባችሁን ያህል ማድረግ ከቻላችሁ ሕዝቡስ የልፋታችሁን ዋጋ እጥፍ ይከፍላችኋል። ይሄንን ደግሞ አይተናል፣ እናውቃለንም። ያኔም የሀገሪቱ የመዝናኛ ዘርፍ አንድ እርምጃ ወደፊት ይራመዳል።
ደግሞ አንድ ነገር ልጠቁማችሁ። በምንም ይሁን በምን ያገኛችሁትን ዝና ለመልካም ሥራ ተጠቀሙበት። ምድራዊ ስማችሁን ሽጡና ሰማያዊ ስም ግዙበት። ለምሳሌ ሁላችሁም በየሙያችሁ ማለትም ዘፋኞች በዘፈናችሁ፣ ተዋናዮችም እንደዚሁ በፊልማችሁ ወይም በቲያትራችሁ ሀገሪቱን እየዞራችሁ ገንዘብ ብታሰባስቡና ከቻላችሁ አንድ ትልቅ የበጎ አድራጎት ድርጅት ብትከፍቱ ካልቻላችሁ ደግሞ  እነ ሙዳይን፣ መቄዶኒያን፣ ጌርጌሴኖንን  እንዲሁም ሌሎችን ብትረዱ በምድርም በሰማይም የማይጠፋ ስምን፣ የማይደበዝዝ ክብርን ታገኛላችሁ። ነገር ግን አንድም ሕዝባዊ ስሜት ሳይኖራችሁ ሁልጊዜ በየሚዲያው የህዝብ ነኝ እያላችሁ በዚህ ምስኪን ሕዝብ ባትቀልዱበት መልካም ነው።
ይህ የኔ ብቻ ሳይሆን የብዙሀኑ ሰው አመለካከት ይመስለኛል። ማሳሰቢያ፦ ይሄ ጽሁፍ 97% የሚሆኑትን ብቻ እንጅ ሁሉንም አርቲስቶች አይመለከትም። በሰከነ መንገድ በአመክንዮ ተንተርሶ መወያየት ደግሞ የእድገት ምልክት ነውና ጦማሬን ያነበባችሁ ሰዎች የተሰማችሁን ማንኛውንም ስሜት ከነምክንያታችሁ ጻፉልኝ። ከተሳሳትሁ ለመታረም ዝግጁ ነኝ።
ዘጸአት ለኢትዮጵያ!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች